Latest

ads header

ዜና

የመተከል እና ካማሺ ዞኖች ፀጥታ በፍጥነት ሊታረም ይገባል - ኢሰመኮ


የመተከል እና ካማሺ ዞኖች የፀጥታ ሁኔታና የነዋሪዎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚወሰዱ እርምጃዎች በተሻለ ፍጥነት ሊተገበሩ ይገባል ሲል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። 

ኢሰመኮ ከጥር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በክልሉ ሴዳል ከተባለው ወረዳ የሸሹ ነዋሪዎች ነገሩኝ ብሎ ባወጣው መረጃ በሚደርሱ ተደጋጋሚ ጥቃቶች በርካታ ነዋሪዎች ተፈናቅለዋል፣ ከመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ዝግ ሆነው ቆይተዋል ብሏል። 


ከመስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ “የጉሙዝ ታጣቂዎች” በወረዳው የሚኖሩ ሕጻናትን፣ ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ ወደ 145 የሚገመቱ የጉሙዝ ብሔር ተወላጅ አባወራዎችን ማገታቸውን ከዚሁ የሸሹ ሰዎች ለኮሚሽኑ አሳውቀዋል ብሏል። ታጣቂዎቹ “ዓላማችንን አልደገፋችሁም”  በሚል ምክንያት አፍሰው እንደወሰዷቸውና “መርሻው” እና “ኤክፈት” ተብሎ በሚጠራ አካባቢ እንዳገቷቸው መናገራቸውንም ኮሚሽኑ ገልጿል።



ከታጋቾቹ መካከል “ቢያንስ ሁለት ሰዎች በታጣቂዎቹ መገደላቸውንና” ቀሪው “በአስከፊ ስቃይ ውስጥ የተያዙ” መሆናቸውንም ኮሚሽኑ ያወጣው ሪፖርት ይጠቅሳል። በተጨማሪም መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም.  በደረሰ ጥቃት 5000 የሚሆኑ የሴዳል ወረዳ ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለጊዜው በወረዳው መስተዳደር ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ ተብሏል። 


ኮሚሽኑ እደረግኩኝ ባለው ክትትል፣ ከመስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ በአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች እና በታጣቂ ኃይሎቹ መካከል “ውጊያ” የተካሄደ ሲሆን ከመስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ ነዋሪዎችን ወደ ዳሊቲ ከተማ ለማሸሽ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ማወቁን ተናግሯል። 


በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በካማሺ እና በመተከል ዞኖች በተደጋጋሚ የሲቪል ሰዎችን ሕይወት መጥፋትና የንብረት ውድመት እየደረሰ ቢሆንም በፌዴራል እና ክልል መንግሥታት የተወሰዱት እርምጃዎች በቂ አለመሆናቸውን የጠቀሰው ኮሚሽኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል ሁለንተናዊ መፍትሔ እንዲፈለግም ጠይቋል።

ምንም አስተያየቶች የሉም