Latest

ads header

ዜና

የወሲብ ጥቃት ሴቶችን ለመርሳት በሽታ ይዳርጋል - ጥናት

የወሲብ ጥቃት ሴቶችን ለመርሳት በሽታ ይዳርጋል - ጥናት

ሰሞኑን ከአሜሪካ የወጣ አንድ ሳይንሳዊ ጥናት እንዳመለከተው የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ለአንጎል ውስጥ የደም ዝውውር ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። ይህም «ዲሜንሲያ» ተብሎ ለሚጠራው የመርሳት በሽታ ከፍተኛ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል። 


የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በዓለም ዙሪያ ከ736 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሴቶች በማያውቁት ወይም በቅርብ ሰው ቢያንስ አንድ ጊዜ ተገድደው ይደፈራሉ። 


ከነዚህም ውስጥ 30 በመቶ የሚሆኑት ከ15 ዓመት ዕድሜ በላይ የሆኑ ሴቶች የዚህ ጥቃት ሰለባ ናቸው። 


ሆኖም ሙያዊ ምክርና የህክምና ክትትል የሚያገኙት 40 በመቶ ያህሉ ብቻ። 

የወሲብ ጥቃት ሴቶችን ለመርሳት በሽታ ይዳርጋል - ጥናት

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ወሲባዊ ጥቃቶች ከአካላዊ ጉዳት በተጨማሪ ለሀፍረት እና መሸማቀቅ፣ ለስሜት መረበሽና ድብርትን ለመሳሰሉ የሥነ-ልቦና ቀውሶች  ሊዳርግ እንደሚችል  የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልፁ ቆይተዋል።


አዲስ አበባ በሚገኘው ሞሽን ተብሎ በሚጠራው የስነ-ልቡና የምክር አገልግሎት እና የስልጠና መስጫ ተቋም ምክትል ዳይሬክተርና በማማከር አገልግሎት የበርካታ አመታት ልምድ ያላቸው አቶ ብርሃኑ ራቦ ለዶቼቬለ እንዳሉት እርሳቸው ወደ ሚያማክሩበት ድርጅት በጥናቱ የተነሳው ችግር ያጋጠማቸው ሴቶች ይመጣሉ።  


ጥናቱ በአሜሪካ የፒትስበርግ ዩኒቨርስቲ የሥነ -አእምሮ ፕሮፌሰር በሆኑት እና የጥናት ቡድኑን በመሩት  ርቤካ ቱርስተን አማካኝነት በጎርጎሪያኑ መስከረም 22 ቀን 2021  በአንድ የውይይት መድረክ ላይ የቀረበ ሲሆን፤ በቅርቡም በሥነ-አእምሮ ጉዳይ በሚያተኩረው « Brain Imaging and Behavior» በተባለው የሳይንስ መፅሄት ላይ የስሜት ቀውስ በአንጎል ውስጥ የደም ፍሰትን ሊያስተጓጉል  እንደሚችል ሰፍሯል። 


ፕሮፌሰር ቱርስተን እና እርሳቸው የሚመሩት የምርምር ቡድን  ጥናቱን ያካሄዱት በአሜሪካ መካከለኛ ዕድሜ ባላቸው 150 በሚሆኑ  ሴቶች ሲሆን፤ ከነዚህም ውስጥ 68% በመቶ የሚሆኑት የወሲብ ጥቃትን ጨምሮ ቢያንስ በህይወታቸው አንድ ጊዜ  የስቃይ ሰለባ የሆኑ ናቸው። 


23 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በወሲብ ጥቃት ሳቢያ ከፍተኛ የስሜት ቀውስ  የደረሰባቸው መሆኑን ጥናቱ አመልክቷል። 


በእነዚህ ሴቶች ላይ በተደረገው ጥልቅ ጥናትም የወሲብ ጥቃት በሴቶች የአእምሮ ጤና ብቻ ሳይሆን ለአንጎል ጤናም አደገኛ መሆኑን  ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል። 


በዚህ ሁኔታ ሴቶች ከጥቃቱ  በኋላ ከሚያጋጥማቸው ከፍተኛ ጭንቀት፣ የመንፈስ  መታወክ ፣እንዲሁም ድብርት  የመሳሰሉ የአእምሮ ጤና እክሎች በተጨማሪ  ለመርሳት በሽታና የአንጎል የደም ዝውውር ችግርን ለመሳሰሉ  በሽታዎች በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጋለጡ ጥናቱ አመልክቷል።


እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ደግሞ ችግሩ በማህበረሰቡ ብዙም በግልፅ የማይወራበትና የምክር አገልግሎትና መፍትሄ የማይገኝበት በመሆኑ ችግሩ የከፋ መሆኑን ባለሙያው አቶ ብርሃኑ ያስረዳሉ።


በጎርጎሪያኑ  2018 ዓ/ም   ቀደም ሲል በተደረገ ሌላ  ጥናትም ፣ የወሲብ ጥቃት ያጋጠማቸው ሴቶች በመንፈስ ጭንቀት ወይም በመረበሽ ስሜት የመያዝ እና ጥቃት ካልተሰነዘሩባቸው ሴቶች በበለጠ ታመው የመተኛት እድላቸው ከፍተኛ ነው። 


ከመንፈስ ጭንቀቱ በተጨማሪ  የእንቅልፍ መዛባት እንዲሁም አጠቃላይ ደካማ የጤና ሁኔታ ታይቶባቸዋል። 


የአእምሮ ጤና መታወክን ተከትሎ በሚመጣው  የእንቅልፍ እጦት ሳቢያ  ደግሞ ሴቶቹን ለልብ ህመም፣ ለደም ግፊት ፣ ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ እና ለከመጠን በላይ ውፍረት እንደሚዳርግ  ተረጋግጧል።


ተመራማሪዎቹ በእነዚህ ቀደምት ሳይንሳዊ የጥናት ውጤቶች ላይ ተመስርተው ባካሄዱት አዲስ ጥናትም  የአዕምሮን እና የሌሎች የጤና ሁኔታዎችን በሚመለከትበት መረጃ ለመሰብሰብ የአእምሮ መታወክ እና እንደ ስትሮክ ያሉ የአንጎል ችግሮችን እና የሚያስከትሉትን አደጋዎችን ቀድሞ ለመለየት  የሚያገለግለውን «ኤም አር አይ»የተባለውን የአንጎል ምስል ማንሻ  ምርመራ ተጠቅመዋል። 


በምርመራው  መሰረትም  የአንጎል ችግር ከመከሰቱ በፊት ጠቋሚ  ምልክቶች የሆኑት ጥቃቅን ነጭ ቁስ አካላት  በእንግሊዝኛው  የ«white matter hyperintensity» መጠን ጥቃት በደረሰባቸው ሴቶች ላይ ከፍተኛ መሆኑን በጥናቱ አረጋግጠዋል። 


ተመራማሪዎቹ በስሜት መረበሽ እና የአንጎልን ደህንነት በሚወስኑት በነጭ ቁስ አካላት እንዲሁም በጥቃቱ መካከል ተያያዥነት ይኖር እንደሁ ለማወቅ ባደረጉት  ምርምርም ችግሮቹ በቀጥታ ከጥቃቱ ጋር የሚያያዙ መሆናቸውንም የምርምር ቡድኑ በጥናቱ ደርሰንበታል ብሏል። 


ባለሙያው እንደሚሉት  ምንም እንኳ ጥቃት ለደረሰባቸው ሴቶች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በኢትዮጵያ እጅግ ጥቂት ቢሆኑም  እነዚህን መሰል  አዳዲስ ጥናቶች ላይ በመመርኮዝ መፍትሄ መስጠት ጠቃሚ ነው። 


የእሳቸው ድርጅትም በተቻለው መጠን ይህንኑ እያደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።



ተመራማሪዎቹ አያይዘውም አዲሱ ሳይንሳዊ ጥናት ያረጋገጠው ተጨማሪ ጉዳት የችግሩ ስፋት ምን ድረስ መሆኑን ያመላከተ ሲሆን፤ የሴቶች ጥቃትን የበለጠ መከላከል እንደሚያስፈልግም የሚያሳስብ ነው ብለዋል።  


እንደ ምርምር ቡድኑ የመርሳት በሽታ ፣የአንጎል የደም ስር ችግር ወይም ስትሮክን የመሳሰሉ  ችግሮች ከመከሰታቸው  በፊት እንደ መጀመሪያ ጠቋሚ ምልክት የሚያገለግሉትን ነጭ የአንጎል ጥቃቅን ህዋሳት ሁኔታን  ቀድሞ ማወቅ ይቻላል። 


በመሆኑም ጥናቱ ከፍተኛ አደጋን ቀደም ብሎ ለመለየት አስፈላጊ መረጃ ነው ተብሏል። 


ከዚህ በመነሳት  ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች  ወደ ከፋ ችግር ሳይገቡ ጥናቱ ባረጋገጣቸው በእነዚህ የበሽታው ጠቋሚ ምልክቶች በመታገዝ ቀድሞ መፍትሄ መፈለግ የተሻለ መሆኑንም ጥናቱ ጠቁሟል። 


ለዚህም የመንግስታት ቁርጠኝነት ወሳኝ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ጨምረው ገልፀዋል።

ምንም አስተያየቶች የሉም