በካርቱም ከታጣቂዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 5 የሱዳን የደህንነት አባላት ተገደሉ
ታጣቂዎቹ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተነግሯል
በካርቱም ከታጣቂዎች ጋር በተደረገ የተኩስ ልውውጥ 5 የሱዳን የደህንነት አባላት ተገደሉ፡፡
የደህንነት አባላቱ የአይ ኤስ የሽብር ቡድን አባላት ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ከተጠረጠሩ ታጣቂዎች ጋር በከፈቱት ተኩስ ነው የተገደሉት፡፡
የሱዳን የብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አምስት አባላቱ በተሰነዘረባቸው ጥቃት ህይወታቸው ማለፉን እንዳስታወቀ ኤፒን ጠቅሶ አል ዐይን ዘግቧል።
አባላቱ የተገደሉት የአይ ኤስ የሽበር ቡድን አባላት ናቸው በሚል የተጠረጠሩ ሰዎችን ለመያዝ ስምሪት ላይ እያሉ በተከፈተ የተኩስ ልውውጥ እንደሆነም ተገልጿል።
በዚህ አደጋ ተሳትፈዋል በሚልም 11 የውጭ አገራት ዜግነት ያላቸው ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን የአገሪቱ የደህንነት ተቋም ገልጿል።
አይኤስ የተሰኘው የሽብር ቡድን እስካሁን በሱዳን ለተሰነዘረው ጥቃት ሃላፊነት መውሰዱን ያልገለጸ ሲሆን የሱዳን መንግስት ግን ጥቃቱ በዚህ የሽብር ቡድን ደርሷል ብሏል።
አሜሪካ ከዚህ በፊት አይኤስ የሽብር ቡድን በሱዳን ሊንቀሳቀስ እና ጥቃት ሊሰነዝር ይችላል የሚል ስጋት እንዳላት ገልጻ ነበር።
በደህንነት አባላቱ ሞት ማዘናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ገልጸዋል፡፡
ጥቃቱ “ከሸፈ” የተባለው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በተፈጸመ በሳምንቱ የተፈጸመ ነው፡፡
ይህ የሃገሪቱን ዲሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት እንዳያስተጓጉለው ተሰግቷል፡፡
በእርግጥ የአል ቃይዳውን መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን ጭምር በአንድ ወቅት አስተናግዳ በነበረችው ሱዳን መሰል የታጣቂ ጥቃቶች እምብዛም የተለመዱ አይደሉም፡፡
ሆኖም በኬንያ እና ታንዛኒያ ከተፈጸሙ የሽብር ጥቶች ጋር በተያያዘ አሜሪካ ሱዳንን በጥቁር የሽብር መዝገብ ላይ ጭምር አስፍራት እንደነበር ይታወሳል፤ ምንም እንኳን በቅርቡ ከዝርዝሩ ብትወጣም፡፡
ባሳለፍነው ዓመት ወርሃ መጋቢት ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ምንም አስተያየቶች የሉም