Latest

ads header

ዜና

"ደስ ይላል መስከረም" ✍️ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ)



 "ደስ ይላል መስከረም" 

በግርሻ'ጣይ ሰርዶ ነቅሎ በሚያዚያንሽ ተርበጥብጦ 

በግንቦት ሐሩር ተቀቅሎ በፀሐይ አብስሎ በዝናብ አብቅሎ

ከወዳጅ ከዘመድ ተቀላቅሎ 

ባዝራን ከአህያ አዳቅሎ

በባለበርሸት ሽልም በቅሎ

ተፈናጦ አብሮ ገስግሶ

ጅራፍ ግርፊያ ሆያ ሆዬ-ቡሄ በሉ ተጫውቶ

ኪዳነ ምሕረትን አንግሶ-ደግሞ በወሩ ለአስተሮዬው

ግሼን ማሪያም እማአርያም ደጀሰላም ደርሶ ለመሳለም

"እዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ

ዐደይ ለምለም ለኔ እንዳንቺ የለም..."

እያሉ ንጥቂያ ---

ከጀንበር መፍለቂያ እሥከ ጀንበር መጥለቂያ

አለላ ነቅሎ ባሕር እንጉዳይ

ጀግና ሰውገዳይ

አካል እንጉዳይ

እያሉ ሲያንጎራጉሩ !

ደስ ይላል መስከረም ! ! ! 

ቡቃያው ጣል ከንበል ሲስ

ሽሩባዋ ወርዶ እንዲያ ሲዘናፈል

ልቤ እንደበቆሎ ያድራል ሲ ፈ ለ ፈ ል

በቀጭን ተሰርታ ሥትል ዘንከት ዘንከት

ጃሎ ሲል ሊያነጋ አገር በመለከት

ለመስቀል ጠንስሶ በማድጋ ገንቦ ለእንግዳ ቀንሶ

በሞቴ አፈር ስሆን እያለ ሲያጋፍር

ጥርስ እንጎቻ አስፍቶ አሞጭ በመሰለው እርጎ ፍርፍር

እንኳን ሳቅ ጨዋታው ድብድቡ ልፊያው

ድገሙኝ ያሰኛል ሰፈፍ የለሽ ሞገድ መደዶ ዘር ዜማ ሲቆረቆር ክትፊያው

ደስ ይላል መስከረም ! ! !

የሽንብራ ሸት እየጠረጠሩ 

የልጅነት ሚዜ 'ኧረ አይዋ ክንዴ' እያሉ እየጠሩ

አብሮ ወፍ ጥበቃ ማማ ላይ ተሰቅሎ

ካፊያውን በገሳ በአንድ ተጠልሎ

እሳት አቀጣጥሎ በቆሎ ጠባብሶ

አየሁ አላየሁም...ሰማሁ አልሰማሁም

በላልቶ አፍ አብሶ

ለስለሶ አስፈትሎ የ'ናት ኩታ ለብሶ

ላዋቂ ተልኮ ለልጅ ተጎናብሶ

ደስ ይላል መስከረም ! ! !

እንደቢራ ቢሮ አበባ ለአበባ ዐደይ እንቡር እንቡር

በፍቅር ለመክረም -

ደስ ይላል መስከረም ! ! ! 

ወፉ ከነ ጎጆው እሥከ መናጆው

ንቡ ከነ ቀፎው መረባ ከነ እርፎው

በዐደይ ለምለም ክብር ለመስከረም ክብር 

ቅዱስ! ቅዱስ! ቅዱስ!

የዓመት አሥራት ሊያፈስ

ሊያስገባለት ግብር

በዝማሬ ሲያብር

አንጄት ሲበረብር

ደስ ይላል መስከረም ! ! !

ተዋዶ ወዶ ተወሕዶ ያንጀት ተፈቃቅዶ

ባንድ አብሮ ለመክረም

ደስ ይላል መስከረም ! ! ! 

ለቅኔ ዘረፋው ጠፈፍ ሲል ፈፋው

የቆሎ ተማሪ ያ ተመራማሪ

የወላዲት አምላክ የድንግል አዝማሪ

ያ ደበሎ ለባሽ!

በእግዚትነ ማሪያም፥ እባካቹህ እባሽ እባካቹህ ቁራሽ

እ ያ ለ ሲለምን

ከጥንቅሹ ቅንጥሽ ማሩቴ ባይሰጠው

አይቀር መደንገጡ አራሽ አባ ወራሽ ማብላት ያሰለጠው

የማይለወጠው

በዐይኑ እየመዘነ በልቡ እማይመርጠው

ገሩ ባላገሩ

ያ ባለሞፈሩ...ያ ባለዘገሩ

በሞቴ ነው ቋንቋው ስሞት ነው ነገሩ

ደስ ይላል መስከረም ! ! !

ወዶ ተወሕዶ ያንጀት ተፈቃቅዶ

አንድ ልብ አቅዶ

አንድ ላይ ለመክረም

ደስ ይላል መስከረም ! ! !

...

ጥቅምትና ኅዳር ቢያዋውል ምንጭ ዳር

ታኅሳስና ጥር ዐውድማ አስለቅልቆ ጥሪት እሚያስቋጥር

የካቲት መጋቢት መኸር አስከትቶ ቢያበስል እንደ ዐቃቢት

ሚያዚያና ግንቦቱ ተርቲበኛው ቀርቦ ወርዶ ራከቦቱ

የላም ልጅ በዋንጫ ቢቀርብ ሥልባቦቱ

ሰኔ ሐምሌ ነሐሴ እንደ ቄስ ምናሴ

እያረበረበ ደግሞ እየወረበ

ሰማይ በበረቀ ታርሶርሶ ሲስረቀረቅ

ከራሱ እስኪታረቅ

...ሁሉም እንደ ግብሩ

ሁሉም እንደ ሙያው!

አሥራ ሁለቱም ወር

እዮሃ አበባዬ መስከረም ሲጠባ

ያኔ ነው ገቢያ 

ያኔ ነው መታያው ...

ያኔ ነው ማባያው ...

ደስ ይላል መስከረም ! ! !


✍️ ሙሉጌታ ተስፋዬ (አያ ሙሌ)

ምንም አስተያየቶች የሉም