በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ እየተባባሰ ነው - ተመድ
በሰሜን ኢትዮጵያ በተለይ ትግራይ ክልል ውስጥ ያለው የሰብዓዊ ቀውስ ሁኔታ እየተባባሰ መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ የኢትዮጵያ ተጠባባቂ አስተባባሪ የሆኑት ግራንት ሊየቲ ትናንት በሰጡት መግለጫ ትግራይ የነበረው የእርዳታ ምግብ ክምችት ባለፈው ነሐሴ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ማለቁን አመልክተዋል።
“ለችግሩ መፈጠር ምክንያት የሆነው ሰብዓዊ አቅርቦቶችን ለማሳለፍ የሚወስደው ረጅም ጊዜ ነው” የሚሉት ሊየቲ የኢትዮጵያ መንግሥት ያልተገደበ ተደራሽነትን እንዲፈቅድ ጠይቀዋል።
ለችግሩ ህወሓትን ተጠያቂ የሚያደርገው የኢትዮጵያ መንግሥት ወቀሳውን አይቀበልም።
አንድ ዓመት የተጠጋው በህወሓትናን በፌደራሉ መንግሥት መካከል በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ሚልዮኖች ለረሀብ በሺዎች የሚቆጠሩትን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት አጋልጧል።
በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነቱ ክልሉን ከመሰረተ ልማት አገልግሎት አቅርቦት ውጭ አድርጎታል፤ ይህም የነዋሪዎችን ህይወት አክብዶታል። ጦርነቱ በዓፋርና አማራ ክልሎችም ጉዳት እያስከተለ ነው።
ህወሓት የፌዴራሉ መንግሥት የትግራይን ህዝብ ለመጉዳት አገልግሎቱን አቋርጧል ሲል፤ የፌዴራል መንግሥት በበኩሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎቱን እንድናስጀምር ህወሓት ጦርነቱን መቆም አለበት ሲሉ ይደመጣሉ።
ምንም አስተያየቶች የሉም