Ticker

6/recent/ticker-posts

ኮረም ከተማ አሁንም በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ናት ሲሉ የትግራይ አመራሮች ገለጹ

ኮረም ከተማ


ከትግራይ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ የሆኑት የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ለቢቢሲ በሰጡት ቃል ኮረም አሁንም በኛ ቁጥጥር ሥር ናት ብለዋል።


የኢትዮጵያ መንግሥት  ማክሰኞ ጥቅምት 8/2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ የከተማ ውስጥ ውጊያ ሳያካሂድ የትግራይ ከተሞች የሆኑትን ሽረ፣ አላማጣ እና ኮረምን መያዙን አስታወቆ ነበር።


ይሁንና ፕሮፌሰር ክንደያ "መንግሥት ኮረምን ተቆጣጥረናል ማለቱ ከእውነት የራቀ ነው" ብለዋል፣ ትናንት ረቡዕ ምሽት ጥቅምት 9፣ 2015 ዓ.ም ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ።


ፕሮፌሰር ክንደያ ‘ኮረም አሁንም ያሉት የኛ ኃይሎች ናቸው’ ካሉ በኋላ ይሁንና ከኮረም አቅራቢያ በበርካታ አካባቢዎች ብርቱ ውጊያ እየተደረገ እንደሆነ አልሸሸጉም።


በአካባቢው የግንኙነት መስመሮች በመቋረጣቸው ቢቢሲ ኮረም ከተማ በማን እጅ እንዳለች ለጊዜው ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።


የትግራይ ኃይሎች ሰኞ ዕለት ባወጡት መግለጫ የፌዴራል ኃይል ሽረ ከተማን መቆጣጠሩን መግለጻቸው ይታወሳል።


በትግራይ እየተደረገ ባለው መጠነ ሰፊ ጦርነት ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳቶች እየደረሱ ስለመሆኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየገለጹ ይገኛሉ።


የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽነር ትናንት በሰጡት መግለጫ ‘በአየር ድብደባና ከባድ መሣሪያ ጥቃት በርካታ ንጹሐን መሞታቸውን፣ ንብረት መውደሙን የሚያትቱ ሪፖርቶች እየደረሷቸው እንደሆነ አብራርተዋል።


በሲቪሎች እና በሲቪል ተቋማት  ላይ ሆን ብሎ ጥቃት ማድረስ የጦር ወንጀል ተደርጎ ሊታይ እንደሚችል ኮሚሽኑ አስጠንቅቋል።


የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ አሁን ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው ካሉ በኋላ ይህ በድጋሚ ያገረሸው ጦርነት ከመጀመሩ በፊት እንኳ 13 ሚሊዮን የሚሆኑ ዜጎች በትግራይ፣ አማራና አፋር ምግብ እርዳታን ይሹ ነበር ብለዋል።


ሁሉም ተዋጊ ወገኖች የሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ሊያደርጉ ይገባል ሲሉ መክረው ነበር።


አንቶኒዮ ጉተሬዝ ይህን ከማለታቸው አንድ ቀን በፊት በትዊተር ገጻቸው በኢትዮጵያ ያለው ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል ብለው ነበር።


ይህን ለማቆምም ተዋጊ ወገኖች በፍጥነት ንግግር እንዲጀምሩም ማሳሰባቸው ይታወሳል።


በጄኔቫ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠሪ ትናንት ባወጣው መግለጫ ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በሰላማዊ ሰዎች ሞት ዙርያ ያወጡት መግለጫን በመንቀፍ የኢትዮጵያ ሠራዊት በዚህ ረገድ ለሰላማዊ ዜጎች ልዩ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ አረጋግጧል። 


የትግራይ ኃይሎችና የፌዴራል መንግሥት ለአምስት ወራት ያህል በተናጥል ተኩስ ካቆሙ በኋላ ነበር ከ55 ቀናት በፊት በድንገት ውጊያው ያገረሸው።


ባለፉት ሁለት ዓመታት በጦርነቱ የኃይል ሚዛንም ሲለዋወጥ ነው የቆየው።


ይህን ግጭት ለመፍታት በአፍሪካ ኅብረት መሪነት ሲደረግ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ፍሬ ሳያፈራ ቀርቷል።


ይህ ጦርነት ዳግም ከማገርሸቱ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ሁለቱ ወገኖች በደቡብ አፍሪካ ተገናኝተው ንግግር እንደሚጀምሩ ተስፋ ተጥሎ ነበር።

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች