Ticker

6/recent/ticker-posts

በአዲስ አበባ የውጭ አገራት ገንዘቦች በሕገወጥ አሠራር ሲመነዘርባቸው ይታዩ የነበሩ ወይም በጥቁር ገበያ ይሳተፉ የነበሩ በዛ ያሉ ሱቆች ታሸጉ



በአዲስ አበባ የውጭ አገራት ገንዘቦች በሕገወጥ አሠራር ሲመነዘርባቸው ይታዩ የነበሩ ወይም በጥቁር ገበያ ይሳተፉ የነበሩ በዛ ያሉ ሱቆች ታሸጉ።


በአዲስ አበባ ከተማ በተለይ በብሔራዊ ቴአትር እና አካባቢው ፣ ስታዲየምና ዙሪያ ገባው ፣ ጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ፊት ለፊት እንዲሁም ኢትዮጵያ ሆቴል አካባቢዎች በሚገኙ ልዩ ልዩ አነስተኛ ሱቆች ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች አላፊ አግዳሚው ምንዛሪ ይፈልግ እንደሆን በግላጭ ይጠየቅ ነበር።


በእነዚህ አካባቢዎች በተለይ ወጣቶች በብዛት ሲሳተፉበት በሚስተዋለው ይህን መሰል ሕገ ወጥ ተግባር የአሜሪካ ዶላርን ፣ የአውሮፓ መገበያያ ገንዘብ ዩሮን፣ ፓውንድንና እና ሌሎች የውጭ አገራት ገንዘቦችን ብሔራዊ ባንክ በየዕለቱ ከሚያወጣው የውጭ አገራት ገንዘብ የምንዛሪ ተመን ከፍ ባለ የተጋነነ ልዩነት ሕገ ወጥ የገንዘብ ምንዛሪ ተግባር ሲፈፅሙ ማየት የተለመደ ዕለታዊ ክስተት ነበር።


ዶይቼ ቬለ በእነዚህ አካባቢዎች ዛሬ ባደረገው ቅኝት አብዛኞቹ ሱቆች በመደዳ በራቸው ላይ ታሽጓል የሚል ማኅተም ያረፈበት ወረቀት ተለጥፎባቸው ተዘግተውና ለወትሮው በርከት ብለው ይህንኑ ተግባር በመፈጸም ይታዩ ከነበሩ ሰዎች መንገዶቹ ጭር ብለው ተመልክቷል።


እነዚህ ሱቆች ሲታሸጉ በአካባቢው የነበረውን ሁኔታ የተመለከቱ ሰዎች ለDW እንደነገሩት እርምጃው ቀይ ቀለም ያለው ወታደራዊ መለዮ ባጠለቁ ወታደሮች ነው ታኅሣሥ 20 ቀን 2014 ዓ. ም ማለትም ያለፈው ረቡዕ የማሸግ እርምጃ በድንገት የተወሰደባቸው።


የዐይን እማኞች እንዳሉት በወቅቱ ይሄንኑ ሕገ ወጥ ሥራ ሲያከናውኑ የነበሩና የተገኙ ሰዎች እርምጃው ድንገተኛ ስለነበር በእነዚሁ የፀጥታ አካላት ተይዘው ተወስደዋል። ወዴት እንደተወሰዱ ግን እንደማያውቁ ገልፀዋል።


ዶይቼ ቬለ ከዚህ በፊት ባደረገው ምልከታ በተለይ አዲስ ከተገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሕንፃ አካባቢ ፣ ከብሔራዊ ቴአትር ፊት ለፊት እንዲሁም ከጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ፊት ለፊት ባሉት ሥፍራዎች የውጭ አገራት ገንዘቦችን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ ብር የሚመነዝሩ ሰዎች በተለያዩ ተሽከርካሪዎች እና በእግር ለዚሁ ተግባር የሚሄዱ ሰዎችን ሲያስተናግዱ፣ ምንዛሪውን ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ የሚሄደው ሰው በፈለገው ቦታ ሄደው ሊያስተናግዱት እንደሚችሉ ስልክ ቁጥር ጭምር እየተለዋወጡ ድርጊቱን በነፃነት ሲከውኑ አስተውሏል።


የውጭ አገራት ገንዘቦች ሕገ ወጥ ምንዛሪ ወይም የጥቁር ገበያ ከወራት በፊት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እንደነበር ይታወቃል።


ሆኖም መንግስት አደረግሁት ባለው ክትትል ኢትዮጵያን ለማዳከም የተደረጉ ሥውር የኢኮኖሚ አሻጥር ሥራዎች አካል መሆኑን ደርሼበታለሁ ሲል ገልፅ በወቅቱ በተወሰደ እርምጃ ከፍተኛ መናር ታይቶበት የነበረው የጥቁር ገበያ የምንዛሪ ተመን መውረዱ ይታወሳል።


ከሰሞኑ በውጪ የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ገብተው አገራቸውን እንዲያግዙ የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገራቸው እየገቡ ይገኛሉ።


ይህንን ሥራ ሲፈጽሙ ይስተዋሉ የነበሩት ሱቆች መታሸግ ከዚሁ ጋር የተገናኘ ሳይሆን እንደማይቀር መገመት ይቻላል።


ምንጭ :- DW

አስተያየት ይለጥፉ

0 አስተያየቶች