ሱዳን በአልፋሻጋ የኢትዮጵያ ጦር ኃይልን "ወረራ" ቀለበስኩኝ አለች
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚወዛገቡበት አል-ፋሻጋ የድንበር አካባቢ የሱዳን ጦር "የኢትዮጵያ ኃይሎች ወረራ" ያለውን እንቅስቃሴ መቀልበሱን አስታወቀ።
"ወታደራዊ ኃይሎች የኢትዮጵያ ኃይሎችን ወረራ ኦም ባራከት አካባቢ ቀልብሰው እንዲያፈገፍጉ አስገድደዋቸዋል" የሚል መግለጫ የሱዳን ጦር የብዙኃን መገናኛ አማካሪ እሁድ እለት አውጥተዋል።
የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሉቴናንት ጄኔራል አብዱል-ፋታህ አል-ቡርሃን የኢትዮጵያ ኃይሎች ሞከሩ ያሉትን "ወረራ" የአገራቸው ወታደሮች የቀለበሱት ቅዳሜ ዕለት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
አብዱል-ፋታህ አል-ቡርሃን የሱዳን ጦር ባለፈው ሳምንት ከተሞከረው መፈንቅለ-መንግሥት በኋላ አገሪቱን እየጠበቀ መሆኑን ያሳያል ሲሉም ተናግረዋል።
ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ በኩል የተሰጠ ምላሽ የለም።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ስለ ጉዳዩ ምላሽ እንዴሰጡ ቢጠየቁም ምላሽ አልሰጡም።
ኦም ባራከት ሱዳን ግዛቴ ነው የሚል ጥያቄ ባነሳችበት እና የኢትዮጵያ ገበሬዎች ያርሱት በነበረው የአል-ፋሻጋ አባቢ የሚገኝ ነው።
በኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና በትግራይ ኃይሎች ውጊያ በተቀሰቀሰበት ወቅት ሱዳን ወታደሮቿን በዚሁ በአል-ፋሻጋ አካባቢ አሰማርታለች።
ሁለቱ አገሮች በግዛት ይገባኛል ምክንያት የገቡበት ውጊያና በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ያላቸው ተቃርኖ ግንኙነታቸውን ይበልጥ አሻክሮታል።
እንግሊዝኛውን ለማንበብ ይህን ይጫኑ

ምንም አስተያየቶች የሉም