Latest

ads header

ዜና

ህወሓት የአፍሪካ ሕብረትን በወገንተኝነት ከሰሰ

 

ህወሓት የአፍሪካ ሕብረትን በወገንተኝነት ከሰሰ


የአፍሪካ ሕብርት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ መሾሙን ተከትሎ ነው ህወሓት ሕብረቱን በወገንተኝነትከሰሰው።


ባለፈው ሳምንት የአፍሪካ ሕብረት ለጦርነቱ መፍትሔ ለመፈለግ እንዲረዳው የቀድሞውን የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆን የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው በሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማህማት ተሹመዋል።


ሕብረቱ ኦሉሴጎን ኦባሳንጆን እንደ አሸማጋይ መሾሙን ካሳወቀ ከቀናት በኋላ አማጺው ቡድን የአፍሪካ ሕብረትን በወገንተኝነት በመክሰስ ጥያቄ አንስቷል።


በአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ ሆነው ተሰየሙት ኦባሳንጆ ቀዳሚ ሥራ ለወራት የዘለቀውና በኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

 

ነገር ግን ይህን በቀጠናው ሰላም፣ ደኅንነትና መረጋጋት እንዲሰፍን እንዲሁም የፖለቲካ ውይይትን ለማበረታታት የሚያደርገው ጥረት ያግዛልተባለው የአፍሪካ ሕብረት ሹመትን ተከትሎ በሕብረቱ አቋም ላይ ከህወሓት በኩል ጥያቄን አስከትሏል።

 

የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ የአፍሪካ ሕብረት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መወገኑን በመግለጽ ባለፉት አሰር ወራት የቆየውን ግጭት ተገቢውን ትኩረት አልሰጠውም ሲሉ ከሰዋል።


የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ሙሳፋኪ ማህማት በትግራይና በፌደራል መንግስቱ የተካሄደውን ጦርነት "ሕግ የማስከበር እርምጃና የትኛውም አገር ቢሆን ሊያደርገው የሚችል ድርጊት ነው።" ብለው ነበር።


በወቅቱም ሊቀመንበሩ በዚሁ ንግግራቸው ምክንያት ተቃውሞና ትችት ገጥሟቸው እንደነበር ይታወሳል።


አቶ ጌታቸው በማኅበራዊ የትስስር ገጾች ላይ እንዳሰፈሩት ህወሓት አሸማጋይ መሰየሙን እንደማይቃወም አመልክተው ነገር ግን ይህ ተልዕኮ ይሳካል ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሽብርተኛ ድርጅት ብሎ ከሰየመው ከህወሓት ጋር ምንም አይነት ድርድር እንደማይኖር ማሳወቁ ይታወሳል።

 

ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወራትን ያስቆጠረው ጦርነት በሰኔ ወር ማብቂያ ገደማ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹የተናጠል ተኩስ አቁሜአለሁ፡፡›› በማለት ሠራዊቱን ከክልሉ ‹‹ካስወጣ በኋላም›› ጦርነቱ ቀጥሎ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳትን እያስከተለ ይገኛል።

 

የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮቹን ከትግራይ ክልል ‹‹ማስወጣቱን ተከትሎ›› የህወሓት ኃይሎች በአጎራባቾቹ የአማራና የአፋር ክልሎች ከገቡ በኋላ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

 

በአሁኑ ወቅትም በአማራና በአፋር ክልል ውስጥ የፌደራል መንግሥት ከክልል ኃይሎች ጋር በመሆን ከህወሓት ኃይሎች ጋር ጦርነት እያካሄዱ ነው።

 

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተወያየበት ጊዜ ዋና ጸሐፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሁሉም አካላት ተኩስ አቁመው ለግጭቱ ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

"ሁሉም ወገን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁሞ ወደ ድርድር መምጣት አለበት። ስለኢትዮጵያ ሲሉ ሰላማዊ መንገድን አማራጭ ማድረግ አለባቸው። ሁሉን አካታች የፖለቲካ ውይይት ያስፈልጋል። የውጭ ኃይሎችም ከአገሪቱ መውጣት አለባቸው" ብለው ነበር።

 

በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለፀጥታው ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር "የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁም ህወሓት እንዲቀበል ጫና መረደግ አለበት" ሲሉ መጠየቃቸው ይታወሳል።

 

ከሳምንት በፊት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍፊ ፌልትማን ወደኢትዮጵያና ሌሎች የአካባቢው አገራት በመምጣት ከከፍተኛ ባለሥልጣንት ጋር መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን ስለጉብኝታቸው እስካሁን በይፋ የተሰጠ መግለጫ የለም።

 

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ ማህማት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦሉሴጎን ኦባሳንጆ፤ የአፍሪካ ሕብረትን የጋራ ጥቅም ለማስከበር ይህንን ወሳኝ ስትራቴጂካዊ ኃላፊነት በመቀበላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ለማስቆም ድርድር እንዲደረግና ሰላማዊ መፍትሔ እንዲፈለግ የተለያዩ ወገኖች ጥሪ እያቀረቡ ይገኛሉ።

 


ምንም አስተያየቶች የሉም