በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቷ በምትታወቀው አገር መስቀልን እና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ ተሸክመው የነበሩ አንድ ኢትዮጵያዊ መነኩሴ፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቷን በሚያፈርስ ጦርነት ከትግራይ አማጺያን ጋር ለመዋጋት ጠመንጃን አንስተዋል።
በዚህ ጦርነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንም ተከፋፍላለች።
"በሁለቱም እዋጋለሁ፤ በጸሎቱ እና ጥይት" ይላሉ አባ ገብረማርያም አደራው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ህወሓትን ለመዋጋት ሁሉም አቅም ያለው ኢትዮጵያዊ እንዲዘምት ጥሪ ማድረጋቸውን ተከትሎ የስማቸው ትርጉጉም የማርያም አገልጋይ የሆነው መነኩሴው አባ ገብረ ማርያም፣ የኢትዮጵያን ሠራዊት ለመቀላቀል ተመዝግበዋል።
በፖለቲካው ተሃድሶው ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር መራራ ቁርሾ መፈጠሩን ተከትሎ በጥቅምት መጨረሻ ጦርነት መቀስቀሱ የሚታወስ ነው።
"አገሪቱ ስትፈርስ ... እና ካህናቱ ሲገደሉ፣ መታገል አስፈላጊ መሆኑን በማመን ወደ መከላከያ ሠራዊት ገባሁ" በማለት አባ ገብረማርያም ለቢቢሲ አማርኛ ተናግረዋል።
እሳቸው በሚኖሩበት የአማራ ክልልም ከሚሊሻው አስቀድመው ሥልጠና ማግኘታቸውንም ያስረዳሉ።
"በጦርነቱ መቁሰልንም ሆነ ሞትን አልፈራም። ሁሉንም ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። ምላክን ብቻ ነው የምፈራው" በማለት ያክላሉ።
ጦርነቱ ሲጀመር የአማራ ክልል ኃይሎች በትግራይ ክልል ውስጥ የነበሩ ግዛቶችን በመቆጣጠራቸው ምላሽ በሚመስል ሁኔታ የህወሓት ኃይሎች በነሐሴ ወር በአማራ ክልል በርካታ ቁልፍ ከተሞችን ተቆጣጥረዋል።
ከእነዚህም መካከልም በ12ኛው እና በ13ኛው ክፍለ ዘመን ከአንድ ወጥ ድንጋይ ተፈልፍለው የተሰሩትንና በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኑባት ላሊበላ ትጠቀሳለች።
"በላሊበላ ከ700 በላይ ካህናት ነበሩ፣ አሁን ግን አካባቢው በህወሓት ቁጥጥር ስር በመሆኑ ምክንያት ምንም ዓይነት መሠረታዊ አገልግሎት እያገኙ አይደለም። ደመወዝም እየተከፈላቸው ባለመሆኑ ችግር ውስጥ ናቸው" በማለት በጎንደር ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ምንይችል መሠረት ይናገራሉ።
ቀለሃዎች በቤተ ክርስቲያኗ ተገኝተዋል
በላሊበላ ምንም ዓይነት ጉዳት ባይዘገብም፣ ምንይችል በክልሉ ከሚኙ ሌሎች በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ገንዘብ፣ ምግብ እና ጥንታዊ የብራና ጽሑፎች እንደተዘረፉ፣ ይህም ህወሓት ለሐይማኖታዊ ስፍራዎችና ባህላዊ ቅርሶች "ተገቢውን ጥበቃ ሳይሰጥ ሁሉን አቀፍ ጦርነት እያካሄደ መሆኑን አመላክቷል" ይላሉ።
የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንም በአምስተኛው ክፍለ ዘመን የተቋቋማው የጨጨሆ መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን ከህወሓት በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ ምክንያት ጉዳት እንደደረሰበት ዘግበዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ጉዳት በደረሰበት በጨና ተክለሐይማኖት ወለል ላይ የጥይት ቀለሃዎች መገኘታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በበኩላቸው በነሐሴ ወር መገባደጃ በደረሰ ጥቃት ከተገደሉት በርካታ ሰዎች መካከል ስድስቱ ካህናት መሆናቸውን ይናገራሉ።
በጦርነቱ ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ብዙ ግፎች መፈጸማቸውን በተደጋጋሚ አስተባብለዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን 43 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቷን ሕዝብ የሚሸፍኑ ሲሆን፣ ይህም በአገሪቱ ውስጥ ትልቁና ከፍተኛ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሐይማኖት አድርጓት ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ በርካታ ምዕመኑን ከፋፍሏል።
የትግራይ የሐይማኖት አባቶች እንደሚሉት በክልሉ ውስጥ ከጎረቤት ኤርትራ በመጡ ወታደሮች የተደገፈ ወታደራዊ ዘመቻ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ 325 ገደማ የሚሆኑ የሐይማኖት መሪዎች እንዲገደሉ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።
አክለውም ከአናሳ ሙስሊም ማህበረሰብ የተወሰኑትን ጨምሮ በጦርነቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ በ12 አብያተ ክርስቲያናት እና መስጊዶች ላይ ጥቃት እንደደረሰ ይናገራሉ።
ዐቢይ የሐይማኖትና የመንግሥት መለያየትን ችላ ብለዋል
በሰሜን አሜሪካ ቤተክርስቲያን ስመ ጥር አባል የሆኑት ካናዳዊው ምሁር ጌታቸው አሰፋ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጥቃቶቹ ትግራዋይን "ለመስበር" እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እና በኤርትራ አጋራቸው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ፊት "እንዲንበረከኩ" የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ ያምናሉ።
በትግራይ ተራሮች ላይ 24 ሜትር የተራራ ከፍታ ላይ የተገነባው የ6ኛው ክፍለ ዘመን ደብረ ዳሞ ገዳም፣ የኤርትራ ወታደሮች የጥንታዊ ብራና ጽሁፎችንና ባህላዊ ቅርሶችን ዘረፉ ከተባሉባቸው ቦታዎች አንዱ ነው።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ጦርነቱ በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ጥልቅ መከፋፈል እንዳስከተለ እና የትግራይ ቅርንጫፍ "መደበኛ ባልሆነ መንገድ የራሱን መንገድ" በመጓዝ ላይ መሆኑን ይናገራሉ።
"በዲያስፖራው በኩል እንኳን ከአሁን በኋላ አብረው መጸለይ የማይፈልጉ አሉ። በኦንታሪዮ [በካናዳ] አንድ ቤተ ክርስቲያን የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ተብሎ ተሰይሟል። በአሜሪካ በፊላደልፊያ ውስጥ እንዲሁም በአውስትራሊያ ውስጥ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቷል" ይላሉ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው እንደሚሉት የጴንጤቆስጤ ክርስቲያን እምነት ተከታይ የሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥትና ሐይማኖት የተለያዩ ናቸው ከሚለው መሰረታዊ የኢትዮጵያ ጽንሰ ሃሳብ አፈንግጠዋል።
"እሳቸው ጦርነቱን እንደ መንፈሳዊ ውጊያ አድርገው ያቀርቡታል። ጦርነቱን ለማቆም ስላለው ዓለም አቀፍ ግፊት ዐቢይ ሲናገሩ፣ አገሪቱ ኢየሱስ በመስቀል ላይ እንዲጠጣ የተገደደውን መራራ ሃሞት ለመውሰድ ፈቃደኛ እንደሆነች እና በመጨረሻም 'እናሸንፋለን' እያሉ ነው" በማለት ያስረዳሉ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው አክለውም "ሰዎች ለሰላም መጸለይ ሲገባቸው በሐይማኖታዊ በዓላት ላይ እንኳን ዐቢይ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ይናገራሉ" ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አማካሪዎች አንዱና በኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች በተለይም በወጣቶች መካከል ብዙ ተከታይ ያላቸው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ህወሓትን "መጥፋት ያለባቸው ሰይጣኖች" ብለዋቸዋል።
"እንደነሱ አይነት አረም በዚህች መሬት ላይ ዳግም መፈጠር የለበትም" በማለት ዲያቆኑ መናገራቸውን የኤኤኤፍፒ ዘገባ ያመለክታል።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ዲያቆኑ ጓደኛቸው እንደነበሩና ጦርነቱ ከተነሳ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መገናኘታቸውን እንዳቆሙ ይናገራሉ።
አክለውም "በትግራይ ውስጥ እየተከናወነ ባለው ውስጥ የእሱን ሚና ተገነዘብኩ። የእሱ ትርክት የዘር ማጥፋት ነው" ይላሉ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የዲያቆኑን አስተያየት "አደገኛ" እና "ጥላቻን ያዘለ" በማለት ካወገዘ በኋላ ዲያቆን ዳንኤል ንግግራቸው የሚመለከተው የትግራይ ሕዝብን ሳይሆን "አሸባሪ ድርጅቱን" ነው ሲሉ ተናግረዋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቃል አቀባይ በትግራይ ደጋፊዎች ዘንድ የተሳሳተ ትርጓሜ እንደነበረ ለኤኤፍፒ ገልጸዋል።
ምንይችል "ጥላቻን" እና "የብሔር ክፍፍልን አስፍኗል" በማለት ህወሓትን ለጦርነቱ ተጠያቂ ያደርጋሉ።
"ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከቀድሞው የአማራ ነገሥታት ጋር የሚመሳሰል የኢምፔሪያሊዝም ራዕይ እንዳላቸው ሲከሱ ይሰማሉ። ይህም ህወሓት ተጋሩዎችን ወደ ውጊያ ለማነሳሳት የተጠቀመበት ግልጽ የብሔር ፕሮፓጋንዳ ነው" ይላሉ።
ፕሮፌሰር ጌታቸው በመንግሥትና በህወሓት መካከል የሚደረግ ውይይት ብቻ ጦርነቱን ሊያስቆም እንደሚችል ያምናሉ።
"ከጅምላ ግድያ እና ረሃብ በኋላ እነሱ መደራደር አለባቸው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ለድርድር እንዲስማማ ጫናውን እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ መሆኑን የተናገሩት የቤተክርስቲያኒቱ ፓትርያርክም ለሰላም ጥሪ አድርገዋል።
"በልብሳችን ላይ የታተመው እና በሰውነታችን ላይ የምንነቀሰው መስቀል ለውበት አይደለም። የመስቀሉ ትርጉም ሰላምና እርቅ እስከሆነ ድረስ ሰላምና እርቅ በመካከላችን እና ከእግዚአብሔር ጋር መጠበቅ አለብን" ብለዋል አቡነ ማትያስ በቅርቡ በተከበረው የመስቀል በዓል።
ነገር ግን አባ ገብረማሪያም ህወሓትን ለማሸነፍ በጦር ሜዳ ላይ ይቆያሉ።
"እስካሁን ድረስ በጸሎት ሞክረናል፣ እናም አሁን በጥይት እናሸንፋለን። የኢትዮጵያን ጠላቶች ቀብረን ኢትዮጵያን አንድ እናደርጋለን" ብለዋል
0 አስተያየቶች